ኢትዮጵያ ረጅም የአገርነትና ተከታታይነት ያለው የመንግሥት ታሪክ ካላቸው ጥቂት አገሮች አንዷ ናት፡፡ የረጅም ዘመን አገርነቷና የተከታታይ በሀወርታዊ መንግሥት ባለቤት መሆኗ፣ በጥንታዊ ሥልጣኔ የቴክኖሎጂ ቅሬቶቿና በራሷ የጽሁፍ ቋንቋ የተገለጸ ነው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙት የአክሱም ሀውልት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት፣ የጎንደር ቤተመንግሥቶችና ልዩ ልዩ ጥንታዊ መገልገያ መሣሪያዎች፣ የረጅም ዘመን ታሪኳ ቋሚ ነቃሾች ናቸው፡፡ በቅርቡ በምሥራቅ ኢትዮጵያ የተገኘው ጥንታዊው የሐርላ ሥልጣኔ መገለጫ የሆኑ የገንዘብ ምስሎች፣ በጉርሱም የተገኙት የጎዳ ሮሪስ፣ ከሐረር ከተማ በስተምሥራቅ የተገኘው የሣካ ሻዐሪፍ ሥዕሎች፣ እንዲሁም በአርኬዎሎጂ ጥናትና ምርምር ከምድር ውስጥ ተቆፍረው የተገኙት የድንጋይ ላይ ጽሑፎች የኢትዮጵያን ረጅም ዘመን የታሪክ ባለቤትነት የሚያረጋግጡ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው:፡