የጐንደሩ ጉዳይ የዐማራውን ኅልውና የማስከበሩ ትግል የመጀመሪያው ምዕራፍ እንጂ የመጨረሻው እንዳልሆነ ይታወቅ!
ሰሞኑን የሞሶሎኒ ዓላማ አራማጅ የሆነው ዘረኛው የትግሬ ወያኔ አረመኔአዊ አገዛዝ፤ ባለፉት 40 ዓመታት በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ በተናጠል፤ በዐማራው ነገድ በጥቅል፤ የሚፈጽመው የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ወንጀል ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋርሯል። በቅርቡም ባካሄደው ዘግናኝና ሰቅጣጭ ግድያና ሥቃይ፣ እስራት፣ እንግልትና የማንነት ነጠቃ፣ የጥቃቱ ሰላባና ዒላማ የሆነውን የወልቃይት፣ የጠገዴና የጠለምት ሕዝብ ትዕግሥት አሟጦ ወደለየለት ሕዝባዊ አመጽ መሸጋገሩን የብዙኃን መገናኛ መሣሪያዎች መዘገባቸው ይታወሳል። የሕዝባዊ አመጹ አነሳስም ሕዝቡ አስቦና አቅዶ ያደረገው ሳይሆን፣ በአባይ ወልዱ የሚመራው የትግራይ ገዥ እና «የትግሬ ነፃ አውጭ ግንባር ሊቀመንበር»፣ «የዐማራ ክልል አስተዳደር» ተብየው ሳያውቅና ሳይፈቅድ፣ አፋኝ ነፍሰ ገዳዮቹን በማን አለብኝነት ወደ ጎንደር ከተማ ልኮ፣ የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ሕጋዊና ሰላማዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አባሎችን በደረቁ ሌሊት፣ ሰርቆና አፍኖ ለመውሰድ ባደረገው የአሸባሪነትና የውንብድና ሥራ፣ ጀግናው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ «የአገዛዝ ሥርዓቱ ያወጣው ሕግ ከሚፈቅደውና ከሚያዘው ውጭ፣ በሌሊት ማንም እንደሌባ አፍኖ ሊወስደኝ አይችልም» በማለት በወሰደው ሕጋዊ የተከላካይነት ርምጃ፣ በተፈጠረው የተኩስ ልውውጥ፣ በቋፍ ላይ ለነበረው የሕዝብ ብሶት፣ አሸባሪውና ወንበዴው ወያኔ ቤንዚን በማርከፍከፉ የተነሳ የተፈጠረ ሕዝባዊ ማዕበል ነው።